በዝርዝር

የእንስላስ ችኩል ተራራ

የቱሪስት መስህቡ አይነት፡ : ተፈጥሯዊ

የቱሪስት መስህቡ ያለበት ቦታ፡: በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ አዲዮ ቀበሌ

በዝርዝር

የስልጤ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቅርስና የተፈጥሮ መስህቦች ባለቤት ነው፡፡ አልቾ ውሪሮ ወረዳ ደሞ በስልጤ ዞን ውስጥ ከሚገኙ 8 ወረዳዎች ለየት የሚያደርጋት የበርካታ ታሪካዊ ስፍራዎች፣ የተለያዩ የባህል ትሩፋቶች፣ ቅርሶችና መስህቦች ባለቤት ስትሆን የእንስላስ ችኩል ተራራ ደሞ ከተፈጥሮዎቹ አንዱ ነው፡፡ የሚገኝበትም ቀበሌ አዲዮ ሲሆን የመስህቡ ርቀት ከወረዳው ዋና ከተማ ቃዋቆቶ 18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ይህን የመስህብ ቦታ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ስነ-ምድራዊና ስነ-ውበታዊ ትርኢቶች የሚታዩበት አካባቢው ተፈጥሮ እንደ መጽሐፍ እየተገለጠች ምትነበብ አካባቢ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የአካባቢውን ስነ-ምድራዊ አቀማመጥ በምናይበት ጊዜ በጣም ልዩና ውብ ማራኪ ተፈጥሮ ረቂቅ ጥበባዊ ችሎታዋን ያሳየችበት እንዲሁም በተንቀሳቀስን ልክ የተለያዩ ገፅታዎችን የምናይበት ድንቅና ማራኪ መስህብ ነው፡፡ የአካባቢውን ልዩ ተፈጥሮ ከራሳቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የአኗኗር ዘይቤዎች አላምደው የተመሰረቱ ጥቂት መንደሮች እዛው እንስላስ አካባቢ ይዘታቸውን ሳይለቁ ተመስርተው ይገኛሉ፡፡ እንስላስ ችኩል የተባለበት ምክንያት የአካባቢ ሽማግሌዎች ሲያወጉ ቁመቱ ረጅም ከመሆኑና ራቅ ብሎ ላየ ሰው ከእውነት እንደተተከለ ስለሚመስል ስያሜውን ከዚህ እንዳገኘ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰዓት ጥቂት የማይባል ክፍሉን ከቡታጅራ ጉብሬ የተሰራው የአስፋልት መንገድ በዝግዛግ መልክ ስለቆረጠው የቀድሞ ሙሉ አካሉን ማግኘት ያዳግታል ቢሆንም ቦታው አሁንም እጅግ ማራኪ ነው፡፡ ሌላው ይህ መንገድ ይሄን ተራራ ቆራርጦ /በዚግዛግ መልኩ አልፎ እንስላስ ችኩል በመድፈሩ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሮዋል፡፡ ሌላውን ደግሞ በዚህ እንስላስ መንደር የምናገኘው የእንስላስ ሸለቋማውን ስፍራ ነው፡፡ ይህ ሸለቋማ ስፍራ አመቱን ሙሉ አረንጓዴ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ አራዊቶች መገኘታቸው ነው፡፡ ከውስጡ ተነስተው ከፍታውን ወይንም ጫፉን መድረስ ብዙ ጉልበትና አቅም እንደሚፈልግ አድቬንቸር ቱር ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ሰው ሄደው ቢጎበኘው እያልን ፅሑፋችንን ቋጨን፡፡

<

© 2026/27 G.C የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ፔጅ . All Rights Reserved